የካናዳ የዜግነት ህግ ማሻሻያ (Bill C-3)፡ ማወቅ ያለብዎ ወሳኝ ነገሮች እና የተሳሳቱ ግንዛቤዎች
- Melaku Abebe
- Feb 5
- 3 min read
ቀን: ፌብሩዋሪ 05፣ 2026

በቅርቡ የካናዳ መንግስት በዜግነት ህጉ ላይ ያደረገው ማሻሻያ ወይም "Bill C-3" በብዙ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ካናዳውያን ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል። ይህ ህግ ለብዙዎች ትልቅ የምስራች ይዞ የመጣ ቢሆንም፣ አንዳንዶች ግን ህጉ የማይፈቅደውን ነገር "ይፈቅዳል" ብለው በተሳሳተ መንገድ ሲረዱት ይታያል።
በዚህ ጽሁፍ ቢል C-3 ምን እንደሆነ፣ ምን እንዳልሆነ እና በተለይም "ልጆቼ ከተወለዱ በኋላ ዜግነት ያገኘሁ ወላጅ ከሆንኩኝ ህጉ ይመለከተኛልን?" ለሚለው ጥያቄ ግልፅ መልስ እንሰጣለን።
ቢል C-3 (Bill C-3) ምንድን ነው?
ይህ ህግ በዋናነት የመጣው ቀደም ሲል የነበረውን "የመጀመሪያ ትውልድ ገደብ" (First-Generation Limit) ለማንሳትነው።
የመጀመሪያ ትውልድ ገደብ ምን ማለት ነው? ከዚህ በፊት በነበረው የዜግነት ህግ መሰረት ከካናዳ ውጪ የተወለደ ካናዳዊ ወላጅ ከካናዳ ውጪ ለሚወልደው ልጅ ዜግነትን ማስተላለፍ አይችልም ነበር፨ ይህ ህግ ዜግነትን ከትውልድ ወደ ትውልድ በደም እንዳይተላለፍ ገደብ የሚጥል ነበር። ገደቡ እንዴት እንደሚሰራ በአቶ አበበ ቤተሰብ ታሪክ እንመልከት፡
ትውልድ 1 (አባት - አቶ አበበ): አቶ አበበ ካናዳ ውስጥ ነው የተወለዱት (ወይም ኢትዮጵያ ተወልደው ወደ ካናዳ መጥተው ዜግነት (Naturalized) አግኝተዋል)። አቶ አበበ የካናዳ ዜጋ ናቸው።
አቶ አበበ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለመኖር ወሰኑ።
ትውልድ 2 (ልጅ - ሳሮን): አቶ አበበ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳሮንን ወለዱ። ምንም እንኳን ሳሮን የተወለደችው ካናዳ ባይሆንም አባቷ (አቶ አበበ) በካናዳ የተወለዱ (ወይም ዜግነት ያገኙ) በመሆናቸው፣ ሳሮን (Automatically) የካናዳ ዜጋ ትሆናለች። ይህ የመጀመሪያው ትውልድ ነው።
ትውልድ 3 (የልጅ ልጅ - ናታን): ሳሮን አድጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀረች እንበል። እዛው ኢትዮጵያ ውስጥ ናታን የሚባል ልጅ ወለደች።
ችግሩ እዚህ ጋር ነው፡ በድሮው ህግ መሰረት፣ ናታን ካናዳዊ መሆን አይችልም።
ለምን? እናቱ ሳሮን ካናዳዊት የሆነችው "በትውልድ" (By Descent) እንጂ በካናዳ ተወልዳ ስላልሆነ ዜግነቷን ለልጇ ማስተላለፍ እንዳትችል ህጉ ይገድባት ነበር። ይህ ነው "የመጀመሪያ ትውልድ ገደብ" የሚባለው።
***ይህ ህግ ወላጆች ከካናዳ ውጪ የነበሩት ለካናዳ መንግስት እየሰሩ ከሆነ እነሱ ላይ አይሰራም፨
ህጉ የሚጠቅመው ለነማን ነው?
ለ"Lost Canadians": ከዚህ በፊት በነበረው ህግ ምክንያት ወላጆቻቸው ካናዳዊ ቢሆኑም እነሱ ግን ከካናዳ ውጪ በመወለዳቸው ብቻ ዜግነት ተከልክለው ለነበሩ ሰዎች።
ይህ ህግ ወደ ኋላ ተመልሶ (Retrospective) ስለሚሰራ፣ ከዚህ በፊት በህጉ ምክንያት ዜግነት ያላገኙ ልጆች አሁን ዜግነታቸው (Automatically) ይመለስላቸዋል።
ቢል C-3 ምን አይደለም? (ይህንን በጥንቃቄ ያንብቡ!)
ብዙ ሰዎች የሚምታቱበት እና ግልፅ መሆን ያለበት ዋናው ነጥብ እዚህ ጋር ነው።
ቢል C-3 ዜግነትን ወደ ኋላ ተመልሶ የሚሰጠው ልጁ በሚወለድበት ጊዜ ወላጁ ካናዳዊ ከነበረ ብቻ ነው።
አንድ ወላጅ ልጁን ከወለደ በኋላ ከሆነ የካናዳ ዜግነት ያገኘው ፣ ልጁ በወላጁ አማካኝነት ወዲያው ዜግነትን አያገኝም።
ለምሳሌ፡-
አቶ ከበደ በ2010 ወደ ካናዳ መጡ።
ልጃቸው ሊሊ በ2008 ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር የተወለደችው።
አቶ ከበደ በ2014 የካናዳ ዜግነት አገኙ።
በዚህ ሁኔታ ቢል C-3 ለሊሊ ምንም አይነት የዜግነት መብት አይሰጣትም። ምክንያቱም ሊሊ በምትወለድበት ጊዜ አቶ ከበደ ካናዳዊ ስላልነበሩ ነው። አቶ ከበደ ዜግነት ያገኙት ልጃቸው ከተወለደች በኋላ ስለሆነ፣ ልጃቸውን በስፖንሰርሺፕ (Sponsorship) ሂደት ነው ወደ ካናዳ ማምጣት ያለባቸው እንጂ በዚህ ህግ ዜግነት መጠየቅ አይችሉም።
ማጠቃለያ፡ ልዩነቱ ምንድን ነው?
ሁኔታ | ህጉይመለከታቸዋል? (Bill C-3) | ምክንያት |
ልጅዎ ሲወለድ እርስዎ ካናዳዊ ነበሩ (በውልደት ወይም በዜግነት) | አዎ | ህጉ ከዚህ በፊት የነበረውን ገደብ ስላነሳ፣ ልጅዎ በውጭ ቢወለድም ዜግነት ያገኛል። |
ልጅዎ ከተወለደ በኋላ ነው እርስዎ ዜግነት ያገኙት | አይመለከትዎትም | ህጉ የሚሰራው በውልደት ለሚተላለፍ ዜግነት (Citizenship by Descent) ብቻ ነው። |
ወደፊት ለሚወለዱ ልጆችስ? (The "Substantial Connection" Rule)
ህጉ ከፀደቀበት ቀን (December 2025) ጀምሮ ወይም ከዚያ በኋላ ከካናዳ ውጭ የተወለዱ ወይም በጉዲፈቻ የተወሰዱ ሰዎች፤ ካናዳዊ ወላጃቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ ከካናዳ ውጭ የተወለደ (ወይም በጉዲፈቻ የገባ) ከሆነ፣ የዜግነት ማረጋገጫ ለማግኘት ወይም ለጉዲፈቻ ልጅ ዜግነት ለማመልከት ሲጠይቁ፣ ካናዳዊ ወላጃቸው ቢያንስ ለሦስት ዓመታት በካናዳ ውስጥ እንደኖሩ ማረጋገጥ አለባቸው።
ማሳሰቢያ፡ ከላይ የተዘረዘሩት ነገሮች በሙሉ የጉዲፈቻ (ማደጎ) ልጆችንም የሚመለከት ነው።
ምን ማድረግ አለብዎ?
ልጆችዎ በዚህ ህግ ተጠቃሚ እንደሆኑ እርግጠኛ ካልሆኑ፣ ወይም የልጆችዎ ጉዳይ "ስፖንሰርሺፕ" ወይስ "ዜግነት በውልደት" እንደሆነ ከተጠራጠሩ፣ ያማክሩን!




Comments