ኤክስፕረስ ኤንቲሪ (Express Entry) - ወደ ካናዳ ለመግባትት ፈጣኑ መንገድ! ማወቅ ያለብን ነገሮች
- Melaku Abebe
- Jan 6
- 3 min read
ጃንዋሪ 05/2026

ካናዳ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ከፍተኛ ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎችን በቋሚ ነዋሪነት (Permanent Residency) ትቀበላለች። ለዚህም ቀዳሚውና ፈጣኑ መንገድ ኤክስፕረስ ኤንትሪ (Express Entry) ይባላል። በዚህ ጽሁፍ ስለ ፕሮግራሙ መሰረታዊ ነገሮች እንመለከታለን።
በቅርብ ጊዜ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ በዚህ ሲስተም በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገራት ዜጎች መካከል ቀዳሚዋ ሀገር ህንድ (45%) ስትሆን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን የያዙት አፍሪካውያኑ ሀገራት ካሜሮን (10%)(በፈረንሳይኛ ቋንቋ ምክኒያት) እና ናይጄሪያ (7%) ናቸው፨ ቻይና በቴክኖሎጂ እንዲሁም ፊሊፒንስም በጤና ዘርፍ የሰለጠኑ ዜጎቻቸውን ወደ ካናዳ ከላኩ ሀገራት ውስጥ ተካተዋል፨
ኢትዮጵያውያን በኤክስፕረስ ኤንትሪ ያላቸው ድርሻ በእርግጠኝነት ባይታወቅም በየዓመቱ ግን ግንዛቤው እየጨመረ በመምጣቱ ቁጥሩ እያደገ ነው የሚል እሳቤ አለ።
ኤክስፕረስ ኤንትሪ ምንድን ነው?
ኤክስፕረስ ኤንትሪ ካናዳ በልምድ፥ በሙያ እና በዕውቀት የዳበሩ ሰራተኞችን አወዳድራ ለመምረጥ የምትጠቀምበት የኦንላይን ሲስተም ነው። ይህ ሲስተም ማመልከቻዎችን በፍጥነት ለማስተናገድ ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ በስድስት ወራት ውስጥ ማመልከቻዎ ውሳኔ የሚያገኝበት ሂደት ነው። በዚህ ሲስተም የሚመረጡ ሰዎች እነሱን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸውን (ሚስት እና ልጆች) በቋሚ ነዋሪነት ወደካናዳ የማምጣት ዕድል ይኖራቸዋል፨
በኤክስፕረስ ኤንትሪ ስር ያሉ ሶስት ዋና ዋና ፕሮግራሞች
Federal Skilled Worker Program (FSWP): በውጭ ሀገር የስራ ልምድ፣ የትምህርት ደረጃ እና የእንግሊዝኛ ወይም የፈረንሳይኛ ቋንቋ ችሎታ ላላቸው ባለሙያዎች።
Federal Skilled Trades Program (FSTP): በ እጅ ሙያ ዘርፎች (ለምሳሌ፦ ኮንስትራክሽን፣ ኤሌክትሪክ...) የሰለጠኑ ባለሙያዎች።
Canadian Experience Class (CEC): በካናዳ ውስጥ ቢያንስ የአንድ ዓመት የስራ ልምድ ላላቸው ሰዎች። ይህ ካናዳ ውስጥ በጊዜያዊ መኖሪያ ፈቃድ እየሰሩ ላሉ የሚሆን ነው።
ለመመረጥ ነጥብ የሚሰጥባቸው መስፈርቶች
ኤክስፕረስ ኤንትሪ በ Comprehensive Ranking System (CRS) በተባለ የነጥብ አሰጣጥ ሲስተም የሚሰራ ሲሆን ነጥብ የሚሰጥባቸው ዋና ዋና ጉዳዮችም፡-
ዕድሜ፦ ወጣት መሆን የተሻለ ነጥብ ያስገኛል (ከ18 እስከ 35)
ትምህርት፦ የዲግሪ ወይም ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ።
ቋንቋ፦ የIELTS ወይም CELPIP (እንግሊዝኛ) ወይም TEF/TCF (ፈረንሳይኛ) ውጤት።
የስራ ልምድ፦ ቢያንስ የአንድ ዓመት ተከታታይ የስራ ልምድ።
የማመልከቻ ሂደት
ወደ ሲስተሙ ለመግባት ከታች የተዘረዘሩትን ጉዳዮች ከመፈፀምዎ በፊት ፕሮግራሙ የሚፈልገውን አነስተኛውን መስፈርት ማሟላትዎን ማረጋገጥ ይኖርቦታል (ይህንን ሊንክ በመጫን እሱን ማረጋገጥ ይችላሉ)
ቅድመ መስፈርቱን ካሟሉ ዋናው ሲስተም ውስጥ ለመግባት ደግሞ የሚከተሉትን ሶስት ነገሮችን ማሟላት አለብዎት፦
የትምህርት ደረጃ ግምገማ (ECA)፦ የትምህርት ማስረጃዎ ከካናዳ የትምህርት ደረጃ አንፃር በምን ደረጃ ላይ እንደሚቀመጥ በWES (World Education Services) ወይም መሰል ድርጅቶች ማስገምገም (ለምሳሌ፦ በኢትዮጵያ ያለዎት ዲግሪ በካናዳም ዲግሪ ተብሎ እውቅና ማግኘቱን ማረጋገጥ)። (በተለምዶ የኢትዮጵያ ዲግሪ በካናዳም እንደ ዲግሪ ይቆጠራል)
የቋንቋ ፈተና (IELTS General)፦ በእንግሊዝኛ ወይም በፈረንሳይኛ ፈተና መወሰድ። ብዙ ነጥብ ለማግኘት በ Listening 8፣ በሌሎቹ ደግሞ 7 (CLB 9) ማምጣት ይመከራል።
የስራ ልምድ፦ ቢያንስ የአንድ ዓመት ተከታታይ የባለሙያ የስራ ልምድ።
የሥራ ቅጥር (Job Offer) ግዴታ ነው?
ለእጅ ሙያ ስራዎች ካልሆነ በስተቀር የሥራ ቅጥር ግዴታ አይደለም።
ለኑሮ የሚሆን ገንዘብ (Proof of Funds)
የሥራ ቅጥር ማግኘት ዋና መስፈርት ባይሆንም በካናዳ ስራ እስከሚያገኙ ራስዎን ወይንም አብረዎት የሚመጡትን ቤተሰብዎን ለማኖር የሚያስችል የገንዘብ አቅም እንዳለዎ ማሳየት ግን ግዴታ ነው። አሁን ላይ ባለው መስፈርት መሰረት በባንክ ሂሳባችሁ ሊኖር የሚገባ ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን፡
ለአንድ ሰው፦ ወደ $15,263 CAD (በግምት 1.7 ሚሊዮን ብር)
ለባልና ሚስት፦ ወደ $19,001 CAD (በግምት 2.1 ሚሊዮን ብር) መሆን አለበት።
ማሳሰቢያ፡ የካናዳ የስራ ፈቃድ እና ተቀባይነት ያለው የስራ ቅጥር ያመቻቹ ሰዎች የገንዘብ አቅም ማሳየት አይጠበቅባቸውም!
ማጠቃለያ - ልዩ ዕድል (Category-based Selection)
Category-based selection ካናዳ ባለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገችው አሰራር ሲሆን፣ በዚህ አሰራር መሰረት የሚከተሉት ሙያ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በሌሎች መስፈርቶች (በእድሜ ወይም በትምህርት) ከፍ ያለ ነጥብ ባያገኙም የማለፍ ዕድላቸውን የሚያሰፋ ነው፦
ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች፡- ካናዳ አሁን ላይ ለፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ልዩ ትኩረት እየሰጠች ነው። (እንደ ካሜሩን ያሉ ሀገራት ተጠቃሚ የሆኑት በዚህ ምክንያት ነው)።
የጤና ባለሙያዎች (Healthcare)፦ ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ፋርማሲስቶች እና ሌሎችም።
STEM (Science, Technology, Engineering and Math)፦ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚሰሩ (ለምሳሌ፡ ሶፍትዌር ኢንጂነሮች እና የዳታ ባለሙያዎች)።
የሙያ ዘርፎች (Trades)፦ እንደ ኤሌክትሪሻን፥ ቧንቧ ሰራተኛ እና ስጋ ቆራጮች (Butchers) ያሉ ባለሙያዎች።
ግብርና እና ትራንስፖርት፦ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች እና በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ።
የካናዳ የኢሚግሬሽን ጉዞ ረጅም ቢመስልም፣ በትክክለኛ መረጃና ዝግጅት የሚሳካ ነው። ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የቋንቋ ውጤታቸውን በማሻሻልና በጊዜ የትምህርት ማስረጃቸውን በማስገምገም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ።

Comments