በእርግጥ ካናዳ ለኢትዮጵያውያን "የሥራ ዕድል" ሰጥታለች?
- Melaku Abebe
- Jan 1
- 2 min read
ጃንዋሪ 01/2026

አሁን አሁን የተለያዩ የቲክቶክ (TikTok) ወይም የቴሌግራም (Telegram) ግሩፖችን ሲመለከቱ፣ እንዲህ የሚሉ ማስታወቂያዎችን በብዛት ማየት የተለመደ ሆኗል፡ "ካናዳ 50,000 ሰራተኞችን በተለይም የጭነት መኪና አሽከርካሪዎችን፥ የጽዳት ሰራተኞችን፥ እርሻ ሰራተኞችን ትፈልጋለች! እንግሊዝኛ ቋንቋ አያስፈልግም! አሁኑኑ ያመልክቱ!" ወዘተ.
ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ ሰዎች "ካናዳ ሥራ አውጥታለች አሉ። እንዴት ነው የምሄደው?" የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ይጠይቃሉ
ካናዳ በተወሰኑ መስኮች የሰራተኛ እጥረት እንዳለባት እውነት ነው። ነገር ግን በእነዚህ የስራ መስኮች ተቀጥሮ ወደካናዳ ለመምጣት ሂደቱ በማህበራዊ ሚዲያ ከሚነገረው በጣም የተለየ ነው።
በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ነገር የካናዳ መንግስት ሥራ አይሰጥም፣ ወይም ሥራ አያከፋፍልም። የሚቀጥሩት የግል ኩባንያዎች ናቸው፡ መንግስት ግን ሂደቱን ያሳልጣል፨
በሁለት መንገድ ወደ ካናዳ ለስራ መምጣት ይቻላል፡ 1. በጊዜያዊነት ወይንም 2. በዘላቂነት
በጊዜያዊነት፡ አንድ የካናዳ ኩባንያ/ድርጅት/ግለሰብ ካናዳ ከሌሎች ሀገራት ጋር ባላት የንግድ ስምምነት ወይንም በሌላ ምክኒያት ካልተፈቀደለት በስተቀር ማንኛውንም ከካናዳ ውጪ የሚኖር የውጭ ሀገር ዜጋ በጊዜያዊነት ከመቅጠሩ በፊት ፣ በመጀመሪያ በሀገር ውስጥ የስራ ማስታወቂያ ማውጣት አለበት፨ በሀገር ውስጥ አመልካች ካላገኘ ለካናዳ መንግስት "ይህንን ሥራ የሚሰራ ካናዳዊ ማግኘት አልቻልኩም" ብሎ ማሳመን አለበት። መንግስትም እውነትም ድርጅቱ በካናዳ ውስጥ ያንን ስራ ሊሰራለት የሚችል ሰው አላገኘም ብሎ ካመነ ከሀገር ውጪ ሰው እንዲቀጥር ፈቃድ ይሰጠዋል። ይህ ሂደት Labour Market Impact Assessment (LMIA) ይባላል። ይህ መንገድ በተለምዶ ዝቅተኛ የስራ ልምድ፥ ቋንቋ እና የትምህርት ደረጃ ላላቸው ሰዎች የሚሆን ሲሆን ብዙውን ጊዜም ደሞዙ አነስ ያለ ነው። በዚህ መንገድ ስራ ለማመልከት የሚፈልጉ ሰዎች እዚህ ዌብሳይት ላይ ሄደው LMIA የተፈቀደላቸው

ወይንም ፍቃዳቸው በሂደት ላይ ያሉ

የስራ እድሎችን ማመልከት ይችላሉ።
በአጠቃላይ የስራ ማስተወቂያውን ከፍተው ወደታች ሲወርዱ የካናዳ ባንዲራ ከተመለከቱ ማመልከት አይችሉም የዓለም (globe) ምልክት ካለው ግን ማመልከት ይችላሉ ማለት ነው።
መረሳት የሌለበት ነገር ይህ መንገድ በጊዜያዊነት ወደካናዳ እንዲመጡ የሚያስችል ሲሆን በዘላቂነት ካናዳ ውስጥ ሊቆዩበት የሚችሉበት ምክኒያት ከሌሎት በስተቀር የስራ ውሎ/ፈቃድዎ እንዳለቀ ካናዳን መልቀቅ ይኖርቦታል።
በዘላቂነት ወደካናዳ ለስራ መምጣት፡ ይህ የስራ እድል ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ የሚያሰጥ ሲሆን መስፈርቱም ከጊዜያዊ ስራ የበለጠ እና ውድድሩም የጠነከረ ነው፨ ይህ ዕድል በተፈላጊ የስራ መስኮች የካበተ ልምድ፥ የትምህርት ደረጃ እና ቋንቋን የሚጠይቅ ነው፨ ይህ የስራ እድል በእጣ መልክ የሚወጣ ሲሆን እጣውም የሚወጣው በእያንዳንዱ መስፈርት የተሻለ ነጥብ ላስመዘገቡ ነው፨ በዚህ ፕሮግራም ለመሳተፍ ብቁ መሆንዎን ለማረጋገጥ ይህንን ሊንክ ይጠቀሙ
(በዚህ ርዕስ ዙሪያ ወደፊት በሰፊው እመለስበታለሁ)
አጭበርባሪዎችን እንዴት እንለይ?
"100% ቪዛ እናስመታለን"፡ ማንም ሰው (ጠበቃ ወይንም አማካሪም ቢሆን) የቪዛ "ዋስትና" መስጠት አይችልም። ውሳኔው የቪዛ ኦፊሰሩ ብቻ ነው።
ትክክል ያልሆነ ኢ-ሜይል አድራሻ- በካናዳ ሁሉም ኩባንያ በሚያስብል ደረጃ የራሱ ድርጅትን የሚገልፅ (@company.com or @company.ca). ኢሜይል አድራሻ አለው፨ የስራው ዕድል jobopportunity2025@gmail.com አይነት ከመሰሉ አድራሻዎች የተላከ ከሆነ መጠርጠር ጥሩ ነው፡:
ክፍያ የሚጠይቅ አሰሪ ፡ በካናዳ ለስራ ክፍያን መጠየቅ ህገ ወጥ ነው፨ በተለይም ደግሞ አሰሪው ለ LMIA ሂደት የከፈለውን $1,000 ዶላር እንዲከፍሉ መጠየቅ አይችልም::
ማጠቃለያ አቋራጭ መንገድ የለም። ሙያ ካለዎት እና እንግሊዝኛ ወይንም ፈረንሳይኛ (ተጨማሪ ዕድል ይፈጥራል) ቋንቋ ከቻሉ፣ ቀጣሪ ማግኘት ይቻላሉ።
የስራ እድልዎን ካመቻቹ በኋላ የስራ ፈቃድ እና ቪዛ ለማመልከት እርዳታ ከፈለጉ ያግኙን!
@ኤምቲኤ የኢሚግሬሽን አገልግሎት


Comments